ከካንሳስ ሲቲ እና አካባቢው የአማራ ማህበር የተሰጠ ታላቅ የደስታ መግለጫ!

የተከበራችሁ የካንሳስ ሲቲ እና አካባቢው የአማራ ማህበር አባላትና ደጋፊዎች በሙሉ በቅድሚያ የማክበር ሰላምታችንን ለመግለፅ እንወዳለን። ማህበራችን የካንሳስ ሲቲ እና አካባቢው አማራ ማህበር በሀገራችን ኢትዮጵያ በጦርነትና በተለያዩ ምክንያቶች ችግር ላይ የወደቀውን ወገናችንን ለመደገፍ የተቋቋመ ግብረ ሰናይ ማህበር እንደሆነ ይታወቃል። ማህበራችን ተቀዳሚ ተግባሩ ተጎጂዎችን መደገፍ ቢሆንም ቅሉ ወገናችን (ነገደ አማራ) እየደረሰበት ያለውን ጅምላ ጭፍጨፋ (Massacre), የዘር ፍጅት (Genocide) እና ተጋርጦበት ያለውን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ እያደረገ ያለውን ትግል በንቃት ሲከታተል ቆይቷል። ሆኖም ግን ላለፉት ዓመታት በታጋይ ወንድሞቻችን መካከል በተፈጠረው አለመግባባት የጠፈጠረው ክፍተት ትግሉ እንዲዳከም እና በወገናችን ላይ እየደረሰ ያለው ስቃይ እንዲራዘም ማድረጉ ሁላችንንም አሳዝኖን ቆይቷል። ሆኖም ግን በየፊናው የሚታገሉ ወንድሞች ባደረጉት ያልሰለሰ ጥረት ልዩነታቸውን ቀርፈውና በጋራ ቆመው ሕዝብን ሊያጠፋ የመጣውን ጠላት ለመመከት እና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በአንድ ጥላ ስር መሆናቸውን ስንሰማ ታላቅ ደስታን አጎናጽፎናል። ስለሆነም ማህበራችን የካንሳስ ሲቲ እና አካባቢው የአማራ ማህበር ለመላው አባላቱ፣ ደጋፊዎቹና ለመላው የአማራ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት ይወዳል፡፡

ለወደፊትም በሚደረገው የተቀናጀ የአማራ ህልውና ትግል የካንሳስ ሲቲ አካባቢው የአማራ ማህበር ከዚህ በፊት ሲያደርገው ከነበረው በላቀ መልኩ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር የአማራን ክልል መልሶ ለማልማት እና የተጎዱ ወገኖቻችንን መልሶ ለማቋቋም ዕቅድ በማውጣት ከወገናችን ጎን ለመቆም ማህበራችን ቃል ይገባል፡፡

በድጋሜ ለመላው በካንሳስ ሲቲ እና አካባቢው የአማራ ማህበር አባላትና ደጋፊዎች እንዲሁም ለመላው የአማራ ሕዝብ እንኳን ደስ አላችሁ፤ እንኳን ደስ አለን እያልን የተሰማንን ልባዊ ደስታ ለመግለፅ እንወዳለን፡፡

ጥር 17/2018 ዓ.ም (01/25/2026 G.C)

የካንሳስ ሲቲ እና አካባቢው የአማራ ማህበር (ካሲአአማ)

Kansas City Area Amhara Association (KCAAA)

Scroll to Top